መግቢያ
ሀገራችን ኢትዮጵያ የሰው ልጆች መብት የተከበረባትና ሁሉንም ብሔር/ብሔረሰቦች በዕኩልነት አቅፋ የምትጓዝ ዴሞክራሲያዊት ሀገር ትሆን ዘንድ በየጊዜው ተነስተው ገና ግብ ያልመቱ የሰላም፣ የዴሞክራሲና የፍትህ ጥያቄዎች እንደ አሸን መፍላት የሀገራችንን ታሪክ የትግልና የመስዋዕትነት ታሪክ አድርጎታል። ለሀገራችን ሉዓላዊነትና ነፃነት ደማቸውን ካፈሰሱት፣ አጥንታቸውን ከከሰከሱትና ክቡር ህይወታቸውን ከሰጡት ጀግኖች አርበኞቿ በተያያዘ መልኩ፤ ለሕዝባዊ መንግሥት ምሥረታና ላልተገደበ የመብት ጥያቄ ደማቸውን ያፈሰሱ፣ አጥንታቸውን የከሰከሱና ክቡር ህይወታቸውንም የለገሡ የትውልድ ሰማዕታት ታሪክ: ቢያንስ የግማሽ ምዕተ-ዓመት ታሪካችን ነው።
ኢትዮጵያ ሀገራችን ወደ ዘመናዊና ፍትሃዊ የዕድገት አቅጣጫ እንድትገባ ከነበረው ጽኑ ፍላጎት በመነሳት፤ በ1920/30ዎቹ በነዶ/ር መላኩ በያንና እነርሱን በመሣሰሉ በጣት የሚቆጠሩ ተማሪዎች እንቅስቃሴ ጥንስሡን የጀመረው የኢትዮጵያ ተማሪዎች ትግል፤ እጅግ ሰፍቶና አድጎ ወደ 1950/60ዎቹ የእነ መንግሥቱና ገርማሜ ነዋይ ዘመን ወስዶን ከዚያም ወደ 1960ዎቹ መጀመሪያ ተሸጋግረን በሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች የተሰለፉበት የእነ ጥላሁን ግዛው እንቅስቃሴ አድርሶን በመቶ ሺህ የሚቆጠረው የዛሬው ትውልድ የዴሞክራሲና መብት ተጋድሎ ያደርሰናል።
በዚህ የዓመታት የትግል ታሪክ በየጊዜው በተከሰቱት አገዛዞች መስዋዕትነትን የከፈሉ የዚያና ያሁኑ ትውልድ አባላት በርካታ ናቸው። በደርግ የአንድ ትውልድ መመተር ርምጃ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ብርቅዬ ወጣቶችን፤ ጎልማሶችንና አገር ወዳዶችን ሀገራችን አጥታለች። ያ ትውልድ ያስመዘገበውን አኩሪ የፍትህ ተጋድሎና የከፈለውንም መስዋዕትነት ለማስታወስና ተተኪው ትውልድ ካለፈው ትውልድ ታሪክ በመቅሰም ለሀገሩና ለሕዝቡ ተሟጋች ብቁ ዜጋ ይሆን ዘንድ መሠረት የሚጥል፡ በያ ትውልድ ስም የሚንቀሳቀስ የትውልድ መታሰቢያ ተቋም ተመሥርቷል። የያ ትውልድ ተቋም ከማንኛውም የፖለቲካ እንቅስቃሴ ነፃ ሆኖ በትግሉ ላለፈው ትውልድ መታሰቢያ ይሆን ዘንድ የትግሉን ታሪክ እውነተኛ መረጃ በማሰባሰብ፣ የተጎዱ ወገኖችን በመርዳትና ለትውልዱ የስም መጠሪያ ይሆን ዘንድ መታሰቢያዎችን በማቆም ላይ ትኩረት አድርጎ በሀገር ቤትና በውጭው ዓለም ይንቀሳቀሳል።
እኛ የዚያ ትውልድ አባላትና የመከራው ገፈት ተቋዳሽ የሆኑት ቤተሰቦቻቸው: ይዘን የተነሳው የፖለቲካ ራዕይና ዓላማ ግቡን ሳይመታ ገና በዕንጥልጥል ላይ ያለ ቢሆንም፤ ያለፍንበት የትግል ታሪክና የተከፈለው መስዋዕትነት ለታሪክ ተመራማሪዎችና ለተረካቢው ትውልድ ባግባቡ ሊተላለፍ ይገባዋል እንላለን። በተለይ ያ አንድን ትውልድ የመተረው የደርግ ነፃ ርምጃና ቀይ ሽብር ጭፍጨፋ የአካል ጉዳት የደረሰባቸውን፣ የሥነ-ልቦና ጥቃት ሰለባ የሆኑትንና ተመልካችና ረዳት ያጡትን የዚያና የዚህ ትውልድ አባላትን በሚቻለን አቅም ለመርዳትና ለመንከባከብ እንሠራለን። ሁኔታዎች ሲመቻቹም፤ ለሀገራቸው አንድነትና ለዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ምሥረታ ደማቸውን ያፈሰሱ፣ አጥንታቸውን የከሰከሱ የዚያና የዚህ ትውልድ ወገኖች በስማቸው ቋሚ መታሰቢያ - ማለትም (ትምህርት ቤቶች፣ ቤተ-መጻህፍት፣ ሆስፒታሎች፣ መንገዶች፣ አደባባዮች፣ ወዘተ.) እንዲሰየምላቸው ያ ትውልድ ተቋም ዋና ተልዕኮው አድርጎ ይሠራል። እኛ የያ ትውልድ አባላት በውስጣችን የሚብሰለሰለውንና ያልተወጣነውን የኅሊና ቁስል ለመቅረፍ የሞራል ብቃቱ አለንና የያ ትውልድን ተቋም ራዕይና ተልዕኮም ከግቡ ለማድረስ ቆርጠንና አንድ ሆነን እንሠራለን።